የምንኖረው ያሰብነውንና ባሰብነው ልክ ነው

የምንኖረው ያሰብነውንና ባሰብነው ልክ ነው

የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት የተለየና የከበረ ያደረገው ማሰብ የሚችል አንጎል ስላለው ነው፡፡ ይህ ውድና ድንቅ አንጎል በውስጡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ መልዕክትን የሚያስተላልፉ ኒዩሮን ሴሎች (neuron cells) ሲገኙ እርስ በርሳቸው ደግሞ ትሪሊዮን ጊዜ ይያያዛሉ፡፡ እነዚህ ኒዩሮኖች (neurons) ሌሎች ማንኛውም የምናስባቸው ነገሮች በቅፅበት ወደ nervous system የማስተላለፍ አቅም አላቸው፡፡ በዘርፉ ያጠኑት አዋቂዎች እንደሚሉት አእምሮአችን በቀን ከ50-70 ሺህ ገፅ የሚሆኑ ሃሳቦችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ታዲያ በዚህ የፈጣሪ ፀጋ በሆነው ውዱና ድንቁ አእምሮአችን እንዴትና ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው?

አብዛኞቹ በምድራችን ላይ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ የሃሳብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሳናስብ በምድር ላይ የሚሽከረከር መኪና መስራት አንችልም፡፡ ሳናስብ በሰማይ ላይ እንደ ወፍ የሚበር አውሮፕላን መስራት የማይሞከር ነው፡፡ ሳያስቡ አለምን ሁሉ የሚያገናኝ ሞገድ (web) መዘርጋት የማይታሰብ ነው፡፡ ሳናስብ አለምን የሚያገናኝ ሞገድ ይቅርና እጃችንን እንኳን መዘርጋት አንችልም፡፡ በአጭሩ በዚህ አለም ላይ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳይፈጠሩ በፊት በሰው ልጆች አእምሮ ታስበው ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ራሱ ይህችን አለም እና እኛን የፈጠረው እንዲሁ ባጋጣሚ ሳይሆን በማሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የሁሉም ነገር መጀመሪያ አጋጣሚ ሳይሆን ማሰብ ነው ማለት ነው፡፡

የሁሉም ነገር መጀመሪያ ማሰብ ነው ካልን ማሰብ ራሱ ምንድን ነው?ማሰብ ማለት አእምሮአችን በአንድ ነገር ላይ እንዲያውጠነጥን (concentrate) ማድረግ ነው፡፡ ሀሳብ ልክ እንደ ቦይ ውሃ በአንጎላችን ውስጥ በኒሮንስ አማካኝነት ይፈሳል፡፡ አእምሮአችን ደግሞ ለዚያ ሃሳብ መስመር ሲያበጃጅለትና ቅርፅ ሲያሲዘው በአንድ ነገር ላይ ማሰብ ጀመርን ማለት ነው፡፡ ያንን ሃሳብ ደጋግመን ባሰብን ቁጥር ድጋሚ ለማሰብና ለማስታወስ በጣም ቀላል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ደጋግመን ስላሰብነው በአንጎላችን ውስጥ መጀመሪያ የራሱ የሆነ መንገድ ሰርቷልና፡፡

በአእምሮአችን ውስጥ አንድን ሃሳብ (አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ) ብዙ ጊዜ ደጋግመን ባሰብነው ቁጥር የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚሀ ስለምናስበው ነገር ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም የምንኖረው ያሰብነውንና ባሰብነው ልክ ነው፡፡ የራሳችን የሆነ ነፃ ፈቃድ ስላለን ስንፈልግ ደግ ስንፈልግ ክፉ ሰው መሆን እንችላለን፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ያለው አስተሳሰባችን ላይ ነው፡፡ ደግ ለመሆን ሳናስብ ደግ መሆን አንችልም፣ ክፉም ለመሆን ሳናስብ ክፉ አንሆንም፡፡ ስለዚህ የእኛነታችን መሰረት አስተሳሰባችን ነው፡፡ እኛነታችን ራሱ ያስተሳሰባችን ውጤት ነው፡፡ እናሸንፋለን ብለን ካሰብን በእርግጥም እናሸንፋለን፣ትልቅም እንሆናለን ብለን ካሰብንም ትልቅ እንሆናለን፡፡ ትልቅ ከመሆናችን በፊት ግን ትልቅ ስለመሆን ማሰብ አለብን፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን! ትልቅ ትልቅ እናስብ ትልቅም እንሆናለን!

ተጻፈ – በዘጸሀት ዘ-ኢትዮጵያ

Did you find this post helpful? Share with your friends.