ከንፈሯ…

ከንፈሯ…

ውድ አንባቢዎቼ… እንዴት ናችሁልኝ? ሰላም ሁኑልኝ! እኔ የምለው… የሰሞኑ መብራት ምንድነው ጉዱ? ባሰባቸው እኮ ጃል! መብራትም እንደ ዋልያ እና ቀይ ቀበሮ “ብርቅዬ እንስሳ” ሊሆንብን ነው መሰል፡፡ እኔ አላማረኝም፡፡ ከምር! ደግሞ ሲጠፋ እንደድሮ ጣል ጣል አይደለም፡፡ በጅምላ! ድርግም! ከቦሌ እስከ መርካቶ ድረስ በአንድ ጊዜ፡፡ ፀጉር ቆራጩም፣ ባለወፍጮ ቤቱም፣ ብረት በያጁም… ዱካ ይዘው ወጥተው ቁጭ ብለው መብራት እስከሚመጣ ወሬያቸውን ይሰልቃሉ፡፡ ግማሽ ቀን ቀረች ማለት… ግማሽ ቀን ሙሉ ወሬ ይወራል ማለት ነው፡፡ የአገሬ የወሬ ፍጆታ በጨመረ ቁጥር “ባለ ሁለት አሃዝ” እድገታችንን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚወትፈው ለምን ልብ አይባልም ጃል?
ይልቅ ባለፈው የገጠመኝን አንድ ነገር ልነግራችሁ ነበር አመጣጤ… እስቲ ከቀኑ መጀመሪያ ልጀምርላችሁ….
.
ተፈጥሮ ብዙ ነገር አድላኛለች ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን አንድ ነገር ነፍጋኛለች፡፡ አዎ… እሱም በጠዋት መነሳት የሚሉት ነገር ነው፡፡ ደግሞ ጥሎባቸው(መቼም ጥሎላቸው አልል…) ቤተሰቤ እንዳለ ከአውራ ዶሮ ጋር ቀጠሮ ያላቸው ይመሰል ገና ፀሃይቱ እንኳን ሰውነቷን አፍታታ ሳትጨርስ ይነሳሉ፡፡ እነርሱ ብቻ ቢነሱ ጥሩ ነበር… በሰላም የተኛሁትን እኔንም ይቀሰቅሳሉ፡፡ እውነት… ከመሰለ መንግስቱ “ኦያያ” ቀጥሎ “ፍሬ….. ተነስ ነግቷል!” የምትለዋን ድምፅ ከሁሉ አስበልጬ እጠላታለሁ፡፡
.
እናላችሁ… ቀኑ ማክሰኞ… እኔም ተኝቼ ህልም እያየሁ ነበር፡፡ ደግሞ ህልም ቢባል ህልም እንዳይመስላችሁ… እውነት ሙሉውን ባስታውሰው ከአቫታር ፊልም በላይ ገቢ የሚያስገኝ ስክሪፕት ሊወጣው ይችላል! ብቻ… በህልሜ… አባቴ ሱቅ ላከኝ፡፡ ሱቅ ስሄድ ባለሱቃችን “ሰንብት” የለም፡፡ በሱ ፋንታ ተክቶ የሚሸጠው ማን ቢሆን ጥሩ ነው? ሮቤርቶ ካርሎስ! አዎ፡፡ ሮቤርቶ ካርሎስ እኛ ቤት ፊት ያለው ሱቅ ውስጥ፡፡ ከዛ… “ዘይት ስጠኝ” አልኩት… ዝም ብሎ ያፈጥብኛል፡፡ አሃ… ለካ ሮቤርቶ አማርኛ አይችልም! የሚለው ሃሳብ በአእምሮዬ እንዳቃጨለ “ፍሬ… ክላስ ይረፍድብሃል፡፡ ተነስ” ብሎኝ እርፍ፡፡ “እንዴ… ምን አባህ ትቀባጥራለህ፡፡ ይልቅ ዘይቱን ስጠኝ…” አልኩት፡፡ ዝም ብሎ ያፈጣል፡፡ ከዛ… ሱቁ ሁሉ መነቃነቅ ጀመረ፡፡
.
ነቃሁ፡፡ ለካ የምትነቀንቀኝ እናቴ ነበረች፡፡ “ፍሬ… ክላስ ይረፍድብሃል፡፡ ተነስ” የሚለውን የእናቴን መልእክት በጆሮዬ ገብቶ በሮቤርቶ ካርሎስ አንደበት ከሰንብት ሱቁ ውስጥ ሰማሁት፡፡ ከህልሙ መቋረጥ በላይ በጠዋት መቀስቀሴ አብሽቆኛል፡፡ እናቴ እኔን ቀስቅሳ ወደስራዋ ሄደች፡፡ ክላሴ ውስጥ ያሉት እቃዎቹ በሙሉ በህብረት… “ተኛ! ተኛ! ተኛ!” እያሉ የሚዘምሩ መሰለኝ፡፡ አንሶላዬ ሳይቀር የከባድ መኪና ጎማ ይመስል ገልጬው መነሳት ከበደኝ፡፡ በተኛሁበት… “እህህህ…..” እያልኩ ለሃያ ደቂቃዎች ከተገላበጥኩኝ በኋላ ግድ ሆኖብኝ ተነሳሁ፡፡ ይባስ ብሎ… በመስኮት በኩል ግቢያችንን ስመለከተው ለሊት ሲዘንብ እንዳደረ ተረዳሁ፡፡ አይይ…. በቃ ቀኑን ሙሉ ደብቶኝ ልውል ነው ማለት ነው፡፡ ደግሞ ያ የተረገመ ትምህርት አለ… ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሙዴ ዜሮ ገባ፡፡ እንደምንም ብዬ ፊቴን ታጥቤ… ቁርሴን በልቼ… ከቤት እየተሳብኩ ወጣሁ፡፡
.
ከሰፈሬ እስከ ፒያሳ ታክሲ መያዣ ድረስ ያለው መንገድ ቅርብ ነው፡፡ ከአስር ደይቃ በላይ አይፈጅም፡፡ እንዲያውም መንገዱን በእግር የሚሄድ ሰው ብዙ ጉዶችን ስለሚያይ መንገዱን በእግር መውጣቱ ይመከራል፡፡ የዛን ቀን ግን ምኑም ሳይጥመኝ ያቺን የአስር ደቂቃ መንገድ በታክሲ ተሳፍሬ የፒያሳ ታክሲ መያዣው ጋር ደረስኩ፡፡ እኛ ሰፈር ከሌሎች ሰፈሮች በተለየ ሁኔታ ጠዋት ላይ ምንም አይነት የታክሲ ወረፋ ስለማይኖር በ “ተራ ጥበቃ” ሰበብ ቆመው ወሬ ለመደሰቅ ለሚያስቡ ወያላዎች አመቺ አይደለም፡፡ አንዲት ኮድ ሶስት ነጭ ታክሲ አጠገብ የቆመ አንድ ጥቁር ወጣት ፊቱን ከስክሶ “ፒያሳ በአቋራጭ” እያለ ይጠራል፡፡ ምናልባት እንደኔ በጠዋት መነሳት የሚጠላ ይሆናል እያልኩኝ ታክሲው ላይ ወጥቼ ወደመጨረሻው መደዳ ወንበር አመራሁ፡፡ ከጥግ በኩል አንዲት ልጅ ረፍዶባት ነው መሰለኝ እዛው ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብላ በመስታወት እያየች ሊፒስቲክ ትቀባለች፡፡ ልብ ብዬም አላየኋትም፡፡ ሄጄ ብቻ ከአጠገቧ ተቀመጥኩና ሞባይሌን አውጥቼ አቀርቅሬ አንድ የጀመርኳትን መፅሃፍ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ልጅቷ ተቀብታ ስትጨርስ መስታዎቷን ቦርሳዋ ውስጥ አስገባችና “ይቅርታ” አለችኝ፡፡ ለምኑ እንደሆነ ግራ ገብቶኝ… ቀና ብዬ ሳላያት እንኳን መፅሃፉ ላይ እንዳቀረቀርኩ “ምንም አይደል” አልኳት፡፡
.
ወያላው ከፊት ወንበር ጀምሮ “በአቋራጭ ስለሆነ ታሪፉ ላይ አንድ ብር ይጨምራል” እያለ እየተከራከረ ተሳፋሪውን አንድ ብር ያስጨምራል፡፡ ተሳፋሪውም በበኩሉ “እንዲያውም በአቋራጭ ሲሆን መቀነስ አለበት እንጂ እንዴት ይጨምራል?” እያለ እየጠየቀና እያዘነ አንድ ብሩን ይጨምራል፡፡ እኔም ትንሽ በአንባጓሮው ከተዝናናሁ ቦሃላ የዋጋው ጭማሪው እኔንም እንደሚያካትት ሲገባኝ ትንሽ ተናደድኩ፡፡ ወያላው እኔ ጋር እስከሚደርስ መፅሃፌን ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡ ወያላው ወደመጨረሻው መደዳ ሲደርስ ከአጠገቤ ያለችው ልጅ ብር ሰጠችውና ወደመስኮቱ አንገቷን አዞረች፡፡ እኔም የራሴን ልከፍል ቀና ስል “አንድ ብር ያስጨምራል የኔ እህት…” አላት ወያላው፡፡ ወደኔ ዞር ብላ “ምን አለኝ?” ብላ ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ልነግራት ዞር ስል ፊት ለፊት ተያየን፡፡
ኮረንቲ እንደያዘው ሰው ሙሉ ሰውነቴን ሲነዝረኝ ተሰማኝ፡፡
.
ሰው ከትልቅ ፎቅ ላይ ሲወድቅ… ወይም መኪና ሲገጭ አይታችሁ ሰውነታችሁ ከራሳችሁ እስከ እግራችሁ ድረስ በድንጋቴ ክው ብሎ ያውቃል? እንደዛ ነው የሆንኩት፡፡
.
እስከማስታውሰው ድረስ በህይወቴ እንዲህ ውብ የሆነች ሴት አይቼ አላውቅም፡፡ በዛ ላይ “ምን አለኝ?” ብላ ስትጠይቀኝ ፈገግ ብላ ነበር፡፡ ውበቷን ልነግራችሁ አልችልም! እኔንጃ… በቃ ሳያት የሆነ ከሰማይ የወረደች ነገር መሰለችኝ፡፡ ለሁለት ሰከንድ ያህል አይኖቻችን ተቆላልፈው ቆዩ… እኔ ግን በዛች ቅፅበት የፊት ገፅታዋን ሸመደድኩት፡፡ የቆንጆዎች ቆንጆ! አቤት ከንፈር! ከቅላቱ ደግሞ ሙልት ማለቱ! አይኗ ራሱ የምሽት ጨረቃ ይመስላል፡፡ ከሶስት ሰው መሃል ተጣብቤ ተቀምጬ የት አባቴ ልግባላችሁ! ይህ ሁሉ ነገር በሰከንድ ውስጥ ተጠናቀቀ፡፡ እሷ ላይም እንደ ኢቲቪ ዜና ባለማመን ብዙ ሳላፈጥባት ቶሎ ብዬ ሳትነቃ “አንድ ብር ያስጨምራል ነው ያለሽ” አልኳት፡፡
.
ለወያላው አስር ብር ሰጠችው፡፡ እኔም የራሴን ልከፍል እጄን ወደ ኪሴ ሰደድ ሳደርግ “የሱን ከኔ ላይ ቁረጥለት” አለች፡፡ “ምን ምን?” አለ ከጭንቅላቴ ውስጥ ያለው የራሴው ድምፅ ባለማመን፡፡ ምንድነው እየተከሰተ ያለው? ወያላውም ግራ ገብቶት “እ?” አለ፡፡ ደገመችው፡፡ “የሱንም ሂሳብ ከሰጠሁህ ላይ ቁረጥለት” አለች በለሰለሰ ድምፅ፡፡ ልበር ምንም አልቀረኝም፡፡ ተግደረደርኩ…
“ውይ! ምንም ችግር የለም እናትዬ! ለምን ትቸገሪያለሽ?”
“ችግር የለውም” አለችና ፈገግ አለች፡፡ አቤት ፈገግታ! አቤት ፈገግታ! ይህች ልጅ ጦርነት ሜዳ ላይ ቆማ ብትስቅ ጦረኞቹ ሁሉ ድፍት ብለው የሚቀሩ መሰለኝ፡፡ ጠዋቱ ዝናባማ የሆነው… ምናልባት ፀሃይቱ በሰው መልክ ወርዳ ይሆን እንዴ?
ከሁሉም በላይ ግን የከንፈሯ ነው፡፡ ቁጭ ኢንጆሪውን! እንዲያውም ኢንጆሪዎች ቢመለከቱት በሃፍረት ቀለማቸው ሳይለቅ አይቀርም፡፡ እንዲህ አይነት ከንፈር እዚህ ምድር ላይ ሊኖር አይገባውም!
አይይ… ብቻ ወከባ ተፈጥሮ በወከባ ውስጥ ልጅቷን በቅጡ እንኳን ሳላዋራት ጠፋችብኝ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? ላንተ አላለውም ይባላል ይህን አይነት ነው፡፡ ለማንኛውም ልጅቷ እንደእድል እንኳን ይህን ፅሁፍ ካነበበችው… ይህችን ጋብዣታለሁ፡፡
.
ከንፈሯን…
ባየው ቀልቶ እንደአኬልዳማ
ያጋደለውን ጎረምሶች የጣር ድምፅ እያሰማ
እይታዬ የሷን ከንፈር ስላልሳተ
ከልቦናዬ ተስማምቶ
ልቤ በምኞት ቃተተ
.
ፀዳሉ ውበቷ ከምናቤ ሰርፆ
በምኞት እያንሳፈፈኝ
እሮብ አርቡን አገደፈኝ
ያንን ከንፈር የሲኦል በር
ሳልገድፍ ያገደፈኝን
ከእግዜሩ ጋር ያጣላኝን
ቀን ወጥቶልኝ ባልቀምሰውም
የማሩን ጣእም የንቦቹን
የያሙን ጣእም የሰማዩን
ቢበልጥ እንጂ አያንሰውም!

ሰላም እደሩ፡፡

ፍሬሰንበት ገ/ዮሃንስ
ጥር 2008

Did you find this post helpful? Share with your friends.