የእንግሊዙ ክለብ ሌስተር ሲቲ የ2 አስርት ዓመታት አስገራሚና አስደናቂ  ጉዞ

የእንግሊዙ ክለብ ሌስተር ሲቲ የ2 አስርት ዓመታት አስገራሚና አስደናቂ ጉዞ

ክቡራን አንባቢዎቼ ዛሬ የማቀርብላችሁ በያዝነው ዓመት ሳይጠበቅ ስላንፀባረቀው አንድ የእንግሊዝ ክለብ ያለፉት 20 ዓመታት ጉዞ ነው። በቅድሚያ ትንሽ ስለ ክለቡ ልበላችሁና ቀጥሎ ወደ ዋናው ቁምነገሬ እመለሳለሁ።

የክለቡ ስም ሌስተር ሲቲ ይባላል፡፡ ክለቡ እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም ሌስተር ፎሴ በመባል ተመሰረተ፡፡ በወቅቱ ይህ ክለብ ፎሴ በሚባል ጎዳና አቅራቢያ ባለ ሜዳ ላይ ይጫወት ነበር። በመቀጠልም ክለቡ በ5 የተለያዩ ሜዳዎች ላይ ተጫውቷል፡፡ እናም በ1890 ዓ.ም የሀገሪቱን የእግር ኳስ ማህበር ተቀላቀለ። በኢኮኖሚና በ1ኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ውድድሮች ለ4 ዓመታት ከ1915 ጀምሮ ተቋርጠው እ.ኤ.አ በ1919 ዓ.ም በድጋሚ በተጀመረ ወቅት ሌስተር ፎሴ ራሱን በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ከውድድሩ አግልሏል። ክለቡም በድጋሚ ሌስተር የከተማነት ደረጃ በተሰጣት ማግስት ሌስተር ሲቲ በመባል እንደአዲስ ተቋቋመ። በመቀጠልም ሌስተር ሲቲ በተለያዩ የሀገሪቱ የሊግ ደረጃዎች ላይ በመጫወት ዛሬ የደረሰበት ውጤት ላይ ሊደርስ ችሏል። እስኪ አሁን 20 ዓመታት ወደ ኋላ፡

ሌስተር ሲቲ እ.ኤ.አ 1996 ዓ.ም የሀገሪቱ 3ኛ ላይ ካለው ሊግ(ዲቪዥን ዋን) ወደ 2ኛው ሊግ ፕሪሚየር ሺፕ ያደገበበት ዓመት ነበር። ለተከታታይ 4 ዓመታትም ከ9ኛ እስከ 13ኛ ደረጃ በመያዝና 2 የሊግ ካፕ ዋንጫ በማንሳት ዘልቋል፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ ከ2001-2007 ዓ.ም ለሌስተር ሲቲ ክለብ አስከፊ ወቅት ነበር። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ክለቡ ወደ ዲቪዥን ዋን የተመለሰበትና ከዚህም ብሶ ወደ 4ኛው የሊግ ደረጃ(ሊግ ቱ) የወረደበት ወቅት ነበር። እ.ኤ.አ 2007-2008 ሌስተር ሲቲ ወደ ታችኛው ሌላ ሊግ የወረደበት አሳዛኝ ክስተት የታየበት ዓመት ሆኗል።

እ.ኤ.አ ከ2008-2013 ዓ.ም ሌስተር ሲቲ የሊግ ዋንን ዋንጫ በውድድር ዓመቱ 4 ጨዋታዎችን ብቻ በመሸነፍ አንስቶ ወደ ከፍተኛው ሊግ ፕሪሚየር ሺፕ ተቀላቅሏል፤ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2010 እና 2013 ዓ.ም በጥሎ ማለፍ ብቻ ሳይሳካለት ወደ 1ኛው ሊግ(የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ) ሳይገባ ቀርቷል።

lester_2

በቀጣይ በ2014 ዓ.ም ሌስተር ሲቲ ከ46 ጨዋታዎች 102 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከዋንጫ ጋር ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተቀላቅሏል። እ.ኤ.አ በ2014-15 የውድድር ዘመን ሌስተር ሲቲ 8 ጨዋታዎች በቀሩበት ቅፅበት ነበር ራሱን ወደ ታችኛው ሊግ ከመውረድ ያተረፈው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ  ይህንኑ አቋሙን በመከተል በ2015-16 ዓ.ም ማለትም በያዝነው የውድድር ዘመን ሌስተር ሲቲ ካደረጋቸው 38 የሊግ ጨዋታዎች 3ቱን ብቻ በመሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል። ይህንንም በማስመልከት የሌስተር ከተማ አሁን ድረስ በፌሽታና ፈንጠዝያ ተሞልታለች፤ እኔም ‘ሌስተር ሲቲ በቀጣይ በተለይ በሊጉና በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ምን ያሳየን ይሆን?’ እያልኩ ፅሁፌን በዚህ ላብቃ።

በቀጣዩ ፅሁፌ የሌስተር ሲቲን የዚህ ውድድር አመት ጉዞ እዳስሳለሁ፡፡

በሽመልስ ጌታቸው

Did you find this post helpful? Share with your friends.