ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እ.ኤ.አ በጥር 29 1947 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰሜን ሸዋ ግዛት ተጉለትና ቡልጋ መንፈስ በሚባል ትንሽ መንደር ውስጥ ለዚህች ዓለም ተበረከተ። ትንሹ ወልደመስቀል የቄስ ትምህርቱን እዛው አካባቢ ከተከታተለ በኋላ ዋና ከተማ ወደሆነችው አዲስ አበባ በመምጣት አስፋው ወሰን ት/ቤት፤ ጥቂት ቆይቶም ስፖርት ላይ በስፋት መሳተፍ ወደጀመረበት ት/ቤት ደጅአዝማች ወንድራድ ገባ። ወልደመስቀል ኮስትሬ እንደ ልጆች እግር ኳስን በደንብ ቢጫወትም ለአትሌቲክስ የነበረው ፍቅር ግን ለየት ያለ ነበር፤ ት/ቤቱንም በ400፣ በ800 እና በ1500 ሜ. ሩጫዎች በተለያዩ ውድድሮች ወክሏል።  እ.ኤ.አ በ1964 በ17 ዓመቱ ነበር ወልደመስቀል ለመጀመሪያ ጊዜ በብሄራዊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ በ800 እና በ1500 ሜ. ውድድሮች ጎልቶ መታየት የቻለው፤ በመሆኑም ለቶኪዮ ኦሎምፒክ በሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ እንዲካተት ተደረገ።

ወልደመስቀል ኮስትሬ በኦሎምፒክ ውድድሩ ላይ ግን በወቅቱ ከሀንጋሪ ሀገር በመጣለት ነፃ የትምህርት ዕድል ምክንያት መሳተፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ያን ጊዜ ወልደመስቀል ከውድድሩ በኋላ ቀጥታ ወደ ሀንጋሪ እንዲሄድ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ቢያስፈቅድም ነገሮች እነዳሰበው ስላልሄዱለት ከቤተሰቡ ጋር በመመካከር ከውድድሩ በመቅረት ጉዞውን ቀጥታ ወደ ሀንጋሪ አደረጎ በዚያም የኮሌጅ ትምህርቱን ለ6 ዓመታት በመከታተል በስፖርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከኮሌጁ ተቀብሏል። ሀንጋሪ ባሳለፋቸው ጊዜያቶችም ኮሌጁን በ5000 እና በ10000 ሜ. ውድድሮች በመወከል የተለያዩ ውድድሮችን አድርጓል።

እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ወልደመስቀል ኮስትሬ ወደ ሀገሩ በመመለስ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የስፖርት አስተማሪ በመሆን ሲሰራ ቆየ፤ በተጨማሪም ወልደመስቀል ኮስትሬ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሏል። በዚህ ወቅት ነበር ወልደመስቀል ኮስትሬ ቼክ ሪፐፕሊክ የተማረውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባን የተዋወቀው፡፡ ትውውቃቸውም ጠንክሮ ወልደመስቀል ኮስትሬ እና ንጉሴ ሮባ ብዙ ልምዶችን ለመለዋወጥ በቅተዋል። በአጭር ጊዜም ወልደመስቀል ኮስትሬ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ተሾመ፤ በወቅቱም ብሄራዊ ቡድኑ ጀርመን ሙኒክ ለሚካሄደው የ1972ቱ ኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅት ላይ ነበር። ማርሽ ቀያሪው በመባል የሚታወቀው ምሩፅ ይፍጠርም በዚህ ጊዜ ነበር ኦሎምፒክ ውድድር ሀ ብሎ የጀመረው።

ወልደመስቀል ኮስትሬ እ.ኤ.አ በ1974 የድህረ ምረቃ ት/ቱን ለመከታተል ወደ ሀንጋሪ በመመለስ በዚያ ለ8 ዓመታት ቆይታ አድርጎ የዶክትሬት ዲግሪውን በስፖርት ፔዳጎጂ በመቀበል ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ወደ ሀገሩ እንደተመለሰም ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም የልብ ጓደኛው ንጉሴ ሮባ ህልፈተ ህይወት ምክንያት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዋና አሰልጣኝነትን እስጋኘበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ተመድቦ ስራውን መስራት ጀመረ።

ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ምንም እንኳን የመኪና አደጋ ቢደርስበትም በክራንች ድጋፍ በመታገዝ  ስራውን በትጋት የሰራ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አባት ና የሀገሩ ታላቅና ስኬታማ አሰልጣኝ ነበር። ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ወጣት አትሌቶችን ነቅሶ በማውጣትና በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶችን በማሳደግ ይታወቃል፤ በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ የወጣቶች አትሌቲክስ ፕሮጅክቶችን በማስተዋወቅና ተገግባር ላይ በማዋል የመጀመሪያው ሰው ነበር።

kostere-2

እ.ኤ.አ በ2006ዓ.ም ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በIAAF የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ በመባል ምስክርነት ሲሰጠው፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ለሀግሪቱ አትሌቲክስ ላደረገው አስተዋፅኦ በርካታ የገንዘብ ሽልማቶችን በተለያዩ ጊዜያቶች አበርክቶለታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድንም በዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ስር በአጠቃላይ 28 ሜዳሊያዎችን ሲያገኝ፤ 13ቱ ወርቅ፣ 5ቱ ብርና 10 ሜዳሊያዎች ደግሞ ነሀስ ነበሩ። ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካደረሱ የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ልጆች መካከል ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ ደራር ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር ተጠቃሾቹ ናቸው።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አባት የሆኑት ህይወታቸውን ሙሉ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገት የሰዉት ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ለረጅም ጊዜያቶች በህመም ቆይተው በ ግንቦት 8 2008 ዓ.ም በ69 ዓመታቸው ይህችን ዓለምና ሀገራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ተሰናብተዋል።

ምንጭ፡ ድሬ ቲዩብ፣ ኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ እና IAAF

Did you find this post helpful? Share with your friends.