ለ2016ቱ ኦሎምፒክ በሪዮ

ለ2016ቱ ኦሎምፒክ በሪዮ

በፈረንጆቹ 2009 ዓ.ም የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ነበር የብራዚሏ ዋና ከተማ ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ በያዝነው ዓመት የሚካሄደውን የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንድታዘጋጅ ተመረጣለች በማለት ለብራዚል ሀገር ብስራቱን ያበሰረው። የዘንድሮውን ውድድር ልዩ የሚያደርገው ነገር ይህ ውድድር በደቡብ አሜሪካ አህጉር ሲካሄድ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። የኦሎምፒክ ጨዋታው እ.ኤ.አ በነሀሴ 5 2016 ተጀምሮ በነሀሴ 21 2016 ፍፃሜውን ያደርጋል፤ በመሆኑም የብራዚሏ ዋና ከተማ ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ 73 ቀን ለቀረው ይህ ውድድር ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። እኛም ለዛሬ የሀገሪቱ ዝግጅት ምን እንደሚመስል ለመዳሰስ እንሞክራለን።

በአጠቃላይ የብራዚል መንግስት ለዚህ ድግስ ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ አስቦ የነበረ ሲሆን፤ በእቅዱ ውስጥ የህዝብ መጓጓዣ ላይ፣ በነበሩት የውድድሩ ማስተናገጃ ቦታዎች ላይ የማሻሻል ስራዎች፣ አዳዲስ ግንባታዎች፣ ላአትሌቶቹ ማረፊያ እና ሌሎችም ስራዎች የተካተቱ ናቸው። የብራዚል መንግስት ግን ሳይታሰብ ወደ 25.9 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ እንዳደረገ ነው የሚነገረው፤ የህም የሆነበት ምክንያት ከፍተኛ የዝግጅት ጥያቄ በነበረው የሀገሪቱ ሁኔታ ምክንያት በመነሳቱ ነው። የብራዚሉ ግዙፍ ስታዲየም ማራካኛ የመክፈቻና መዝጊያ ዝግጅቱን እንዲያዘጋጅ ሲደረግ ጆ ሄላንጅ ስታዲየም ደግሞ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንዲካሄድበት የተወሰነ ስታዲየም ነበር። በሌላ በኩል ማሪያ ሌንክ አኳቲክ ማዕከል የውሀ ዋና እና መሰል ውድድሮች የሚካሄዱበት ቦታ ሆኖ ተመርጧል። በዚህ መልኩ ሁሉም ውድድሮች የሚስተናገዱበት ቦታ ከተለየ በኋላ ነበር ለእያንዳንዱ ማዕከላት እድሳትና አዳዲስ ግንባታዎች መከናወን የጀመሩት።

ከመወዳደሪያ ቦታዎቹና ከአትሌቶች መቀመጫ በተጨማሪ የብራዚል መንግስት በስነ-ስርዓት ማስከበር ዙሪያም ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፤ በተለይም በዋና ከተማይቱ ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ በተደጋጋሚ ስለሚፈፀሙ ወንጀሎች ታላላቅ ስራዎችን ሰርቷል። ብራዚል ለድግሱ የሚመጡ ቱሪስቶችንም ችላ አላለችም፤ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ነበር ሆቴሎቿን ዝግጁ ማድረግ የቻለችው። ከዚህም ባሻገር የሀገሪቱ መንግስት ለአቀባበሉም ሆነ ለመስተንግዶ አልተኛም በሚል መንፈስ ብዙ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በአጠቃላይ የብራዚል መንግስት ወደ 75 ቀናት ገደማ ለቀሩት ለዚህ ታላቅ የዓለማችን ውድድር ብዙ ገንዘብና ጊዜን መስዋዕት በማድረግ ዝግጅቱን አጠናቆ የእንግዶቹን እና የዓለማችንን ታላላቅ አትሌቶች መምጣት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

Did you find this post helpful? Share with your friends.