ቃና ውስጤ ነው

ቃና ውስጤ ነው

ልጅ እያለሁ ዲሽ የለንም ነበር፡፡ የኢትዮጲያ ቴሌቪዥን… ማለቴ የኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደሞ ለህጻናት የሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞች  ውስን ነበሩና ቴሌቪዥን የማየት ፍቅር ስንት ጉድ አሳይቶናል መሰላችሁ? ቅዳሜ ቅዳሜ በታላቅ ፊልም እስከ እኩለ ሌሊት ቁጭ ብለን ጦርነትና ግድያ አይተን ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ ታላቅ ፊልም እርም ያልኩት ‘The mummy’ የሚለው ፊልም ከተላለፈ በኋላ ነው፡፡ አረ በስላሴ!

አሁንማ ሀገር ምድሩ ጣቢያ በጣቢያ ሆኖ ህጻኑም፣ ወጣቱም፣ አዛውንቱም አማርጦ ያያል፡፡ MAX,MBC 3, DUBAI, KBS, KANA, LANA እያለ፡፡ እድሜ ለዚያ ሳህን፡፡ አረ ቃና ብል፡፡ ቃና ሰዉ ተነስቶበታል አሉ፡፡ ቃና ጠላቴ ነው፤ ጠላቴ በቤቴ እያለ፡፡ ለኔ አይነቱ ምስኪን ግን ቃና ጠላቱ ሳይሆን መድሀኒቱ ነው፡፡ እንዴ! “አልወድህም ነው ያለችው፤ ህይወቴን አበላሽተኃል፡፡ ስትለው ጊዜ ማሪቾይ እሱ ደሞ እድል ስጭኝ ያበላሸሁትን ላቃና አላት፡፡” እያልን በቃሲም መካ እንጀራ ከመግባት ተርፈናላ፡፡ እናትና አክስቶቻችን ኮርያውም፣ ቱርኩም፣ ህንዱም፣ ጣሊያኑም እንደአበው እየተረተላቸው፤ እንደጥሌ እየዘፈነላቸው እንዴት አልተገላገልን? እንደውም እኮ ይሄ የሀገራትን ወዳጅነት የሚያጠነክር ነው፡፡ እውነት! ወዳጅ የሚያመጣ ጠላት ይባላል? ደግሞ ግርም የሚለኝ… የተርጓሚዎቹ! ስንቱን ቋንቋ አጥንተውት ነው ልጄ? አጃኢብ ነው መቼም፡፡ እንደው እንዴት እንዴት አርገው ነው እኚህ ልጆች ፊልሙን እንዲህ የሚያሳምሩት?  እውነት ቃና ጠላት ነው? ስንት የሀገር ልጅ እበላለሁ ብሎ እንዴት በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እንደተበላ አይደል እንዴ በዚያች በተደባዳቢዋ ልጅ ታሪክ የሚያሳዩን? (ወይኔ ግን እሷ ልጅ እንዴት ነው ሴትዮዋን የምትወቅጣት? ዝም ብላ እኮ ሰፈሯ ማስተር ሞሪና ቴኳንዶ ክለብ ብትከፍት ያዋጣት ነበር፡፡ ምነው እኛ ሰፈር እንኳ አንድ ልጅ አለ ልጆቹን ከጣሪያ በላይ በማስጮህ ብቻ ገንዘብ የሚሰበስብ፡፡ እውነት! ጡንቻ የለ… አዲስ ጥበብ የለ…ታዲያ ረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበታል ሆነና…)

ደግሞስ ምናለ ከዚያ የህንዱ ፊልም የአዲስአበባ ሴቶች አለባበስ ቢማሩ? ሴቱ ሁሉ እንደታረዘ ህጻን የተቦጫጨቀና የተንጠላጠለ ልብስ ለባሽ ሆነ፡፡ አረ ተው መአት አትጥሩብን ብንል ማን ሲሰማን፡፡ ደሞ የድሮ ቴሌቪዥን ይመስል ዳንቴል መልበስ፡፡ አሁን ዛራን አታዩዋትም? እንዴት ታምራለች በረጅም ቀሚሷ?

እውይ ሞት ይርሳኝ! ያችን ቅዳሜ 12፡00 የምትመጣውን ዲምፕላሟን ልጅ ረስቼያት፡፡ (እውነት ግን ዲምፕሏ እኮ በጥይት የተቦደሰች ነው የሚያስመስላት፡፡) አቤት ደስ ስትለኝ፡፡ ቁምነገር እኮ ነው የምታወራው፡፡ ትንሽ የእጇ መወናጨፍ በዛ እንጂ በቃ ምርጥ ናት፡፡ (ባለፈው እትዬ ፈትለ አየቻት አየቻትና “ምነው ጥርሷ አይከደን ልጄ? ጅል ናት እንዴ?” ስትለኝ “ከፍትፍቱ ፊቱ ብላ እኮ ነው እትዬ” አልኳት፡፡ አልተዋጠላትም፡፡ “አይ ምነው ፍትፍቱ ቢበላ አይሻልም? ፊቱ እኮ ላይጠቅመን እንዲህ እያጠገበ” አለችኝ፡፡ አይ እትዬ…) ከሁሉ ደስ የሚለኝ ደሞ የእኚያ የእንስሶቹ… በፊት ‘NATIONAL GEOGRAPHY’ ላይ ሲቀርብ ምንም ሳይገባን እናይ ነበር፡፡ አሁን እድሜ ለቃና ስንት ነገር ተማርን፡፡ ታዲያ ቃና እንዴት ጠላት ሆነ ብዬ ስጠይቅ ብዙ ገንዘብ ትንሽ ጥበብ የተሞላበትን የፊልም ኢንዱስትሪ ማዳከሙ አንድ ምክንያት ሆኖ ቀረበልኝ፡፡ እናንተዬ ሰው አሯሯጩን ይጠላል? እንዲህ እንዲህ እያልን ካላበረታነው የዚህ ሀገር ፊልም ነገር… ደግሞ ሌላኛው ክስ ሰው የቃናን አጠቃቀም አለማወቁ ነው አሉ፡፡ መቸም… በጅሮንድ ተ/ሀዋርያት ተ/ማርያምን ትዝ አስባለኝ፡፡ እሳቸው ናቸው አሉ “ላልሰለጠነ ህዝብ ዴሞክራሲ አይገባውም፤ አይገባውምም፡፡” ብለው ኢትዮጲያን እንቁልልጭ ዲሞክራሲ ያስባሏት፡፡ የገባው ያልገባውን አስገብቶ አለመግባባትን እናጥፋ እንጂ…? እስከመቼ ነው ሰው መጽሀፉን በተሳሳተ መንገድ ተረዳው ሲባል አይታተም፤ ሰው አሳ መብላት አይችልም ሲባል አሳ አይጠመድ የሚባለው? እውነት ይህ ጣቢያ ጥቅም የለውም? የስራ እድልስ አልከፈተም? የተመልካቹን አይንስ? መቼ ነው ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ የምንማረው? ከተሳሳትሁ አርሙኝ፤ ካጠፋሁ ተቆጡኝ፡፡ ለኔ ግን ቃና ጠላቴ አይደለም፡፡ እንደውም ውስጤ ነው፡፡

በሎዛ አድማሱ

Did you find this post helpful? Share with your friends.