የኢትዮጵያውያን ውዝግብ በሪዮ ኦሎምፒክ የውሃ ዋና ውድድር ተሳትፎ

የኢትዮጵያውያን ውዝግብ በሪዮ ኦሎምፒክ የውሃ ዋና ውድድር ተሳትፎ

እንደሚታወቀው 31ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በላቲን አሜሪካዊቷ ሀገር ከተጀመረ ቀናቶች ተቆጥረው አሁን ወደ ማገባደጃው ላይ ይገኛል፡፡ ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያ በውሃ ዋና ተሳታፊው ሮቤል ኪሮስ ሀብቴ አማካኝነት ለዓለም መተዋወቋ በኢትዮጵያውያን ህዝብና በብዙ የስፖርት ተንታኞች አግራሞትንና ውዝግብን ማጫር የጀመረው፡፡ “እንዴት የአንድ በብዙ የአትሌቲክስ ሩጫ ውድድር ባለድል በመሆን በዓለም ስሙዋ የናኘውን ሀገር ባንዲራ በአንድ ባልታወቀ የጀማሪ አትሌት በኦሎምፒክ ውድድር መድረክ ማስተዋወቅ ይገባል?” የሚል ጥያቄ ነበር በብዙዎች ዘንድ የተነሳው፡፡ የውሃ ዋናው አትሌት ሮቤል ኪሮስ በ100 ሜ. የነፃ ቀዘፋ ውድድር ለመወዳደር ነበር ኢትዮጵያን በመወከል ብዙ ርቀት ተጉዞ ብራዚል የገባው፡፡ ይሁንና ገና ወደ መወዳደሪያ ገንዳ ለመጋባት በሚደረገው ዝግጅት ነበር ኢትዮጵያ ለ2016ቱ የኦሎምፒክ ውድድር ስሟ መነሳት የጀመረው፡፡

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ስፖርት ዘርፍ በማይጠበቅ የሰውነት ቅርፅ ተወዳደሪ ያቀረበች የመጀመሪያዋ ሀገርም አርድጓታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በርካታ የስፖርቱ ቤተሰቢች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ከፍተኛ ውግዘትና ቅሬታን ሲያስደምጡ ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ የሀገሪቱ ጋዜጠኞችም በሁኔታው የተሰማቸውን ለመግለፅና ባለድርሻ አካላትን ለማነጋገር ሞክረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የውጪ ሚዲያዎች አትሌት ሮቤል ኪሮስን የተለያየ ስያሜ በመስጠት በስላቅ ለዓለም አስተዋውቀውታል፡፡ ለምሳሌ ያህል የእንግሊዙ ዴይሊ ሜል “Robel the whale” (“ሮቤል አሳነባሪው”) በሚል ርዕስ ፅሁፉን አስነብቧል፡፡ ሮቤል ኪሮስም በወቅቱ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለቀረበለት ጥያቄም እንዲህ በማለት ነበር መልስ ያቀረበው፡፡ “እኛ ኢትዮጵያውያን ሩጫ እንደምንወድ ሁሉም ያውቃል፤ ሆኖም ግን እኔ ምንም አይነት ሩጫ አልወድም፡፡ በሀገሬ የተለየ ስፖርተኛ መሆንን ነው የምፈልገው፡፡ ለዛም ነው ውሃ ዋናን ምርጫ ያደረኩት፡፡ በቃ እኔ ውሃ ዋናን በጣም አድርጌ ነው የምወደው፡፡” እኔም በግሌ እውነት ይህ የውሃ ዋና ተሳትፎ ኢትዮጵያን ለኦሎምፒክ ውድድር የሚያበቃ ነበር ወይ የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡

ይህን ፅሑፍ በምፅፍበት ወቅትም የሪዮ ኦሎምፒክ ለመጠናቀቅ ጥቂት የሚባሉ ውድድሮች ብቻ ቀርተውታል፡፡ በዚህም መሰረት የሜዳሊውን ሰንጠረዥ አሜሪካ በ39 ወርቅ፣ በ36 ብርና በ33 ነሀስ ሜዳሊያዎች በአጠቃላይ በ108 ሜዳሊያዎች በ1ኝነት ስትመራ፤  ቻይናና እንግሊዝ በ67 እና በ63 ጠቅላላ ሜዳሊያ ብዛት ይከተላሉ፡፡ የሜዳሊያ ሰንጠረዡ በዋነኝነት በወርቅ ሜዳሊያ ብዛት የሚተመን ይሆናል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም በ1 ወርቅ፣ በ1 ብርና በ4 ነሀስ በጥቅሉ በ6 ሜዳሊያዎች 39ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

ድል ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቀሪ የውድድር መድረኮች፡፡

በሽመልስ ጌታቸው

Did you find this post helpful? Share with your friends.