የ2016/17 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን

የ2016/17 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን

በአሁኑ ሰዓት ከሚወደዱ ታላላቅ ዓመታዊ የውድድር መድረኮች አንዱና ዋነኛው የሆነው  የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ ለ2016/17 የአመት ቆይታው በፈረንጆቹ ነሀሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በምሳ ሰዓት ፕሮግራሙ ተጀምሯል። የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአይነቱ ልዩ የሚያደርገው በታላላቅ ክለቦች አዳዲስ የግዙፍ አሰልጣኞች መድረክና የዓለም ሪከርድ የተሰበረበት የተጫዋች ዝውውር የተካሄደበት ሊግ መሆኑ ነው።

በክለብ ደረጃ በሆላንዳዊው አሰልጣኝን ሉዊስ ቫንሀል ባለፈው ዓመት ሲሰለጥን የነበረው ማንቺስተር ዩናይትድ ከቼልሲ የተሰናበቱትን “the special one“ በመባል የሚታወቁትን አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን ሲያስፈርም፤ ማንቺስተር ሲቲም በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና አመርቅቶ በጀርመኑ ባየር ሙኒክ ውጤታማነቱን የቀጠለው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላን አስፈርሞታል። ጁቬንቱስን በጣልያን ሴሪ አ ባለድል ያደረገው ጣሊያናዊው አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ቼልሲን ካለፈው ዓመት የውጤት አለመመቸት ውስጥ አውጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎም ይጠበቃል። እንግዲህ እነዚህ ወርቃማ አሰልጣኞች ዓለማችን አሏት ከሚባሉ አሰልጣኞች መሀከል ዋነኞቹ በመሆናቸው የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የበለጠ አጓጊና ልዩ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዓመት የተጫዋቾች ዝውውር ትልቁና ሪከርድ የሰበረው የፖል ፖግባ ወደ ማንቺስተር ዩናይትድ በ85 ሚ. ፓውንድ ዋጋ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ የተቀላቀለበት አጋጣሚ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ክለብ ጥበበኞቹን ሄንሪክ ሚኪታሪያን ከዶርትሙንድና ዘላታን ኢቭራሂሞቪችን ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን በነፃ ያመጣበት ዋነኞቹ ሲሆኑ ማንቺስተር ሲቲም እንደነ ጉንዶጋንና ኖሊቶ የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል። የአርሰን ዌንገሩ አርሰናል እንደተለመደው በዝቅተኛ የዝውውር ተሳትፎ ወደ አዲሱ ፍልሚያ ተቀላቅሏል። ጀርመናዊው የርገን ክሎፕም እንደነ ሴይዱ ማኔ ያሉ ጎበዝ ተጫዋቾችን በማስፈረም ውድድሩን ለማጠንከር አርሰናልን በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በማሸነፍ ቆርጦ ተነስቷል።

በዚህ ዓመት ከታችኛው ሻምፒዮን ሺፕ ውድድርም 3ቱ ክለቦች ሀል ሲቲ፣ ሚድልስቦሮ እና በርንሌይ ከፕሪሚየር ሊጉ የተባረሩትን ኖርዊች ሲቲ፣ ኒውካስትል ዩናይትድንና አስቶን ቪላን በመተካት የዓመቱን ውድድር ሀ ብለው ጀምረዋል። እንግዲህ በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችን ክስተቶች በመያዝ ዓመቱን የጀመረው ተወዳጁ  የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በጣም አጓጊ እና ብዙ አዳዲስ ክስተቶች የሚፈጠሩበት መድርክ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሽመልስ ጌታቸው

Did you find this post helpful? Share with your friends.