ገዳይ ሲያረፋፍድ

ገዳይ ሲያረፋፍድ

ገዳይ ሲያረፋፍድ ድንቅ የአማርኛ ፊልም ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ከርዕሱ ብንጀምር፤ ፊልሙ መቼቱን ባደረገበት አካባቢ የተለመደ እና በሙሉ ነዋሪዎች ከሚነገር ስነ – ቃል የተወሰደ መሆኑ ካጠራጠሮት አንድን ጎጃሜ  “ገዳይ ሲያረፋፍድ …… “ ይበሉት፡፡

“ ……..ሟች ይገሰግሳል፤

የአንዱ መሠደጃው

የአንዱም ቀኑ ደርሷል”  እንደሚላችሁ አልጠራጠርም።

በልብ አንጠልጣይ የድራማ ዘውግ (gener) የተሠራው ይህ ፊልም የታሪኩን መዳረሻ ጎጃም በማደረግ የአካባቢውን ወግ፣ ባህል፣ ስርዓትና አመለካከት ከግሩም ታሪክ አወቃቀርና አተራረክ(story telling) ጋር ያሳየናል፡፡ የተዋንያኑ የባህሪ መላበስ (characterization) እና የመተወን ብቃት ለብዙ የሃገራችን ተዋንያን (ለአንጋፋዎቹም፤ ለ“አንጋፋ” ነን ባዮችም ጭምር) ምሳሌ እና ማስተማርያ መሆን የሚችል ነው፡፡

እያንዳንዱ ቃለ ምልልስ (dialogue) የተፃፈው በጥንቃቄና በድርጊት ሊገለፅ በሚችል መልኩ እንደሆነ ለመገመት ባያዳግትም ፊልሙን ግን “ፊልም” ያሰኙት መምሰል ብቻ ሳይሆን ሆነው የተወኑት እኚያ ድንቅ ተዋንያን ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በምስል አነሳሱ፣ በድምጽ ቀረፃውና በምስልና በድምፅ ውህደቱ በጣም ተዋጥቶለታል፡፡ መቼቱን ካደረገበት አካባቢ የተገኙ ዜማዎችን፣ እንጉርጉሮዎችንና ሙዚቃን በመጠቀም የተሰራው ማጀቢያ ሙዚቃ (sound track) ፊልሙ ሁሉም “የኔ” ብሎ እንዲያየውና ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እያንዳንዱ ትዕይንት (scene) በሚገባ የሚገልፅ የካሜራ ቦታ ይዞታዎች (angels of shooting )፣ የምስልና የድምፅ ድርደራዎች (arrangement) ያለው ሲሆን ብርሃንና ቀለም ምርጫ እና አጠቃቀሙም በጣም ድንቅ ነው፡፡ የታሪክ አነሳስ እና አጨራሱም አመንክዮአዊ (logical ) በመሆኑ ከብዙ (አንዲት ወዳጄ እንዳለችው “ብዙ ገንዘብ ጥቂት ጥበብ ከሚወጣባቸው” ) የአማርኛ ፊልሞች ልዩ ያደርገዋል፡፡

ፊልሙን ከፊልም ሙያዊ መመዘኛዎች(technical standards) ውጪ ስናየው ደግሞ፤ ማስተላለፍ የቻለው ጥቅል ሃሳብ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ የፊልሙም ጭብጥ (significance) በግልፅ የሚታይና ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ ከማህበራዊ ፋይዳው አንፃር ፊልሙ ሊወክለው የሚችለው የህብረተሰብ ክፍል በመኖሩ ተአሚኒ(realistic) ያደርገዋል፡፡ ይህም የአንድ ህብረተሰብ ውክልና (የእኔ ባይ) እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡

በህብረተሰቡ የሚነገሩ ታሪኮችን፣ ወጎችን፣ የህብረተሰቡን የንግግር ዘይቤዎች፣ ስላቅ፣ ምፀት እና ቁምነገሮችን፣ በህብረተሰቡ ከባድ ዋጋ ያላቸው እሴቶችን እና ክስተቶችን  (እንደ መሀንነት፣ ታማኝነት እና ፈሪያ እግዚአብሄር ያሉትን)፤ ህብረተሰቡ ጀብድ ናቸው የሚላቸውን ድርጊቶች እና የእነዚህ ጀብድ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ያላቸውን አስተሳሰብ (ምላሽ ወይም አፀፋ) ለዛ ባለው መንገድ እያዋዛ እና ፍፁም ስነ-ቃላዊ ጥበብ በተሞላበት ሁናቴ ያቀርባቸዋል – ፊልሙ። የዚህን ፊልም ቅኝት ከማገባደዴ በፊት ግን ከፊልሙ ማስታወቂያ ፖስተር ግርጌ ተፃፈውንና እኔም የምስማማበትን ሀረግ ላንሳት፡፡ እንዲህ ትነበባለች፡ “ገዳይ ሲያረፋፍድ” የአማርኛ ፊልሞች ንጉስ። ይገባዋል – እኔም አልሁ፡፡

ሙሉቀን አንተነህ

Did you find this post helpful? Share with your friends.