በዘንድሮ የሪዮ ፓራ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ የታየ አስደናቂ ፎቶግራፍ አንሺ

በዘንድሮ የሪዮ ፓራ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ የታየ አስደናቂ ፎቶግራፍ አንሺ

ጃኦ ማያ ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው በሪዮ ፓራ ኦሎምፒክ ከታዩ ፎቶግራፍ አንሺዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን አግራሞትን የፈጠረው ነገር ጃኦማያ የሚያነሳቸውን ፎቶዎች ማየት አለመቻሉ ነው፡፡

“ፎቶ ግራፍ ለማንሳት አንተ ማየት አይጠበቅብህም፡፡ የእኔ አይኖች ልቤ ውስጥ ናቸው” ጃኦ ማያ በኢንጌናሆ አትሌቲክስ ስታዲየም የተናገረው ንግግር ነበር፡፡ የ41 ዓመቱ ጃኦማያ ገና በ28 ዓመቱ ነበር በዩቬይቲስ ህመም (የዓይን በአየር መሞላት) ሲሰቃይ ቆይቶ የማየት አቅሙን ያጣው፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ሲታገል ቆይቶ በመጨረሻም ከቅርፃ ቅርፅና አንዳንድ ከለሮች በቅርበት ሆኖ ከማየት በስተቀር ምንም ነገር ማየት አልቻለም፡፡ በብራዚል ሳኦፖሎ ፖስታ ቤት ውስጥ እየሰራ ማያ ከዘራ በመጠቀም የብሬይል ትምህርቱን እየተከታተለ ሳለ ነበር በፎቶግራፍ መመሰጥ የጀመረው፡፡ “ስነ-ፎቶግራፍ በአጠቃላይ የውስጣዊ ንቃትን ይመለከታል፡፡ እናም እኔ ሳስበው ዓለምን እንዴት መገንዘብ፣ ማየትና ስሜቱን መረዳት እንደቻልኩ ማሳየት መቻሌ በእውነቱ ያስገርመኛል” ሲል ማያ ይናገራል፡፡

ማያ በአንድ እጁ ካሜራ በሌላ እጁ ደግሞ ከዘራ በመያዝ ነበር በፓራ ኦሎምፒክ ስታዲየም መድረክ መገኘት የቻለው፡፡ “በደንብ በተጠጋሁ ቁጥር የተወዳዳሪዎቹ ልብ ምትና ኮቴያቸው በደንብ ይሰማኛል፡፡ እኔም ፎቶዎቹን ለማንሳት ዝግጁ እሆናለሁ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በርቀትና ድምፅ ሲበዛ ፎቶዎችን ለማንሳት እቸገራለሁ” ይላል ይህ ብራዚላዊ ፎቶግራፍ አንሺ፡፡ አሁን አሁን ማያ ከትራክና ሜዳ ላይ ወደ ርዝመት ዝላይ ራሱን አዙሮ ከፍተኛ ደስተኝነትን ማጣጣም ሲችል፤ ምክንያቱ ደግሞ እንቅስቃሴዎች በቅርበትና በጥራት በዚህ ውድድር መገኘታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በዚህ ውድድር ወቅት የዓለም ሪከርድ የተሰበረበትን የፈረንሳዩዋን አትሌት ማሪ ሊ ፈር ልክ አሹዋው ላይ በምታርፍበት ጊዜ የነበራትን ስሜት የሚያሳይ ፎቶው ምርጥ ሆኖለታል፡፡

በአንድ ወቅት ማያ ራሱ ወደ ውድድር መግባት ፈልጎ እንደ ነበርና፤ ነገር ግን የውድድሩ ደረጃ በጣም ከፍተኛ እንደሆነበት ይናገራል፡፡ ማያ ስለስፖርት እንዲህ ተናግሯል “ስለእውነት ስፖርት ለእኔ ሁሉ ነገሬ ነው፤ እናም ሁሌ በካሜራ እከተለዋለሁ”::

Did you find this post helpful? Share with your friends.