ሰማይ…

ሰማይ…

“The sky is an infinite movie to me. I never get tired of looking at what’s happening up there.”

ሰማይ ደስ ይለኛል። ንጋት፣ ጧት፣ ከሰዓት፣ ማታ፣ ውድቅት፣ ለሊት… መቼም ይሁን ወደላይ አንጋጦ ሰማዩን ማየት፣ ርቀቱን በዓይኔ መመተር፣ በምንምነቱ መገረም ያስደስተኛል። እንደሰማይ ምስጢር፣ እንደሰማይ ግልጽ ነገር ያለ አይመስለኝም። ለመውደዴ በዕውቀትና በአመክንዮ የሚደገፍ ምክንያት የለኝም። ብቻ ውበቱ ይማርከኛል። ሰማይ “ይሄ ነገሩ ያምራል።” አይባልም። ሰማያዊ፣ ጥቁር፤ ቀላ ያለ፣ ጥቁር ሰማያዊ፣ ቢጫም ቢሆን (ለውጡ ሳይሰማኝ) እወደዋለሁ።

ሰማይ ለብዙ ሃይማኖቶች የፈጣሪያቸው፣ የአማልክቶቻቸው መቀመጫ ነው። የጥንት ግሪካዊያንና ሮማዊያን እነዚየስና ጁፒተርን የሰማይ አምላክ እያሉ ይጠራሉ። የክርስትና ‘ራስ’ የሆነው ክርስቶስም ለደቀ-መዛሙርቱ ስለ ጸሎት ሲያስተምር “… በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ…” ብላችሁ ጀምሩ ይላል። እስልምናም በበኩሉ የአላህ መቀመጫ በሰማይ እንደሆነ ይናገራል። ይህንንም ተከትሎ ሃይማኖተኞች ‘ኤሎሄ ኤሎሄ’ ብለው አንድም ለልመና ሌላም ለምስጋና ወደ ሰማይ ያንጋጣሉ። (ሰማይ የሚለው ቃል ‘ሰማኝ’ ከሚለው ጋር ያለነገር የተመሳሰሉ አይመስለኝም) ሰዎች ሲበደሉ እንባቸውን ወደላይ የሚረጩትም በማስረጃ አቤቱታ ለማቅረብ እንደሆነ ልብ ይሏል።

ሰማይ ከመላው ዩኒቨርስ በስሱ የተቆነጠሩ አካላት (Celestial Bodies) መሰየሚያም ነው። ንጋት ሆኖ ከአድማስ ማዶ ያለች ፀሐይ ሰማዩን በወጋገኗ ሰንጥቃ፣ ሰማዩን ግማሽ ግራጫ ግማሽ ቢጫ ቀለም አልብሳ ስትመጣ የሰማዩ የውበት ውሎ ይባረካል። የታደለ ጎበዝ ከፀሐይ ተነፋፍቆ፣ ከሰማይ ተቃጥሮ ንጋት ላይ ሰማዩ በ’እሳት’ ሲፈካ ያያል። ፀሐይም አታሳፍረውም አንድም በውበቷ ሌላም በሙቀቷ ንጋቱን ታፈካለች። ሰማይም ተኛበት፣ ከድብታው ይነቃል። ፊቱን በጤዛ አብሶ፣ ሰማያዊ ፍካቱን ይመልሳል። ያኔ ማለቂያ አልባነቱ ላይ ዓይናችንን እያንከራተትን እንታዘባለን።

እንደሰሞኑ ያለ ዕድል ፀሐይን ካልገጠማት ደግሞ ፍካቷን፣ድምቀቷን ሲያልፍም ግለቷን ከድፍድፍ ደመና ጋር እንካፈላለን። ቀና ብለን ስናይ ግለቷን በደመና የተነጠቀች ፀሐይ (ምናልባትም በንዴት) የቀላ ዓይኗን ከደመናዎች መሃል እያሾለከች ትጠቅሰናለች። ጉዞ ያደከማት ፀሐይ ወደማደሪያዋ ልትከተት፣ ወደቤቷ ልትሰበሰብ ስትል ግለቷ ሲቀንስ ውበቷ ይደምቃል። “ቻው” ስትለን(ኝ) ታባባለች። ቀስ በቀስ ከአድማሱ እየቀለጠች፣ ከተራራ መኃል ስትፈስ የአድማሱን ሰማይ በመልኳ ትሠራዋለች። በፍካቷ ያደመቀችው ሰማይ ማር ይመስላል፣ ማር ይሆናል። ከማማሩ ላይ ቆንጥረን ጥፍጥናውን በቀመስን ያስብላል።

ከዚህ ሁሉ ትዕይንት በኋላ የፀሐይ መከተት ጨለማን ያነግሠዋል። ግን ጨለማም ቢሆን በ’ውበት ሳይዋጋ ለምን እነግሣለሁ?’ ያለ ይመስላል። ሰማዩ የጥቁረቱን ካባ ሲደርብ ብቻውን አይደለም። ጨለማነቱን የሚያስረሱ፣ የውበት ፈርጦችን አንጠልጥሎ ብቅ ይላል። በጥቁር ደረቱ ላይ የጨረቃ ድሪ ሰቅሎ፣ በመላ አካላቱ ላይ ደግሞ በክዋክብት ፈርጥ ደምቆ ይታያል።

የማታ ሰማይ ባሕርን ለማድመቅ ጨረቃን የሚቀድም ያለ አይመስልም። በወር ዑደት ራሷን እየወለደች፣ ሲሻት እየጠፋች፣ ካሻት ደግሞ መልኳን እየቀያየረች ማማር ታውቅበታለች። ያሰኛት ቀን እንደውብ ኮረዳ ከወገቧ ገባ ብላ፣ ቀጭን ብርሃን ለብሳ ትወጣለች። ያማራት ጊዜ ደግሞ ግማሽ ፊቷን ድቅድቅ አለት አልብሳ፣ ግማሹን በብርሃን ሙላት አጎናጽፋ ትከሰታለች። ቀን የሞላላት ሰሞን በአለት ኮሮጆዋ ውስጥ ከፀሐይ የተዋሰችውን ብርሃን ጠቅጥቃ፣ የፀሐይ ታናሽ ወንድም መሆኗን ለማስመስከር ሰማዩን በፀዳሏ ታደምቀዋለች። እንዳሻት ብትሆንም ግን ወደሰማዩ ማዕድ አንጋጠን ከብርሃኗ፣ ከፍካቷ፣ ከውበቷ በዓይናችን፣ በልቡናችን ለመቅመስ አታታክትም፤አትሰለችም። እንደፀሐይ ማቃጠል ስለማያውቃት ብቻ ሳይሆን የጨለማ ጊዜ የውበት ምርኩዝ ስለሆነችም ከሥሯ የተሰለፈ ሁሉ በቃኝን አያውቅም፣ የማንጋጠጥ ድካም እንጂ ሌላ አቃቢ አያገኘውም።

ሌላ የምሽቱ ሰማይ ድምቀት ክዋክብት ናቸው። ቀኑን ሙሉ ከፀሐይ ውጪ ሌላ የማያበቅለውን ጠፍ ሰማይ በምሽት ክዋክብት ይዘሩበታል። የጨለማው ግዝፈትን፣ የሰማዩን ድፍድፍ ጥቁረት በውበት የሚያስረሱ የብርሃን ዛጎሎች ናቸው። ክዋክብቱ አንዳንዴ ብዙ ሌላ ጊዜ ጥቂት ይሆናሉ። ገና ሰማዩ መጥቆር ሲጀምር አንድ፣ ሁለት እያሉ፣ እየተጠራሩ ይወጣሉ። ጨረቃ ያለች ቀን የጨረቃ ውበት ጋሻ-ጃግሬ ሆነው ይፈካሉ። አቀማመጣቸውም እንዳፈተታቸው ነው። ባይተዋርነትን የመረጡት ነጠል፣ ራቅ ብለው፣ መሰብሰብ ያሻቸው ዳመራ እንደሚያበራ ከብበው፣ ሰልፍ ያማራቸው በሰልፍ ተሰድረው፣ እንደፍንጭት ጥርስ ተራራቁም ተቀራረቡም ሳይባሉ የሚቀመጡም አሉ። ክዋክብቱ የሕፃን ልጅ ፈገግታ ይመስላሉ። የሚያሳሱ ዓይነት ናቸው። አንዳንዶቹ ስስ፣ ሌሎች ደማቅ (የመፍነክነክ) የብርሃን ፈገግታ ይረጫሉ። አንዳንዴ ደግሞ (ካደለህ) ተወርዋሪ ኮከብ የሰማዩን አርብ ከልብህ ጋር ሰንጥቆት ያልፋል። (ከሰሞኑ እኔም አንድ አይቻለሁ ሁላ!)

“The sky is the daily bread of the eyes.” (ሰማይ የዓይን የዕለት እንጀራ ነው።) ይላል Ralph Emerson ዕለት ተዕለት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ (በፀሐይ መሥረቅ አልያም ግባት፣ በጨረቃ ድምቀት ካልሆነም በክዋክብት ውበት) ለዓይናችን የውበት ምግብ ከመሆን ቦዝኖ አያውቅም። ለአፍታ ቀና ስንል ልብ የሚሞላ ሐሴት ያሸክመናል። ክፍያ ተጠይቆበት አያውቅም፣ የትም መሄድ አያሻውም። ቀና ማለት ብቻ ነው ክፍያው፣ ማንጋጠጥ ብቻ ነው ጉዞው።

ዳዊት ብርሃኑ

Did you find this post helpful? Share with your friends.