የአርብ ማታ ዳንኪራ…

የአርብ ማታ ዳንኪራ…

ግቢ  ያስቀኛል፣  ይገረመኛል፤ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ መልክ በወጣቱ የዕድሜ ክልል ቁልጭ ብሎ የሚታይበት መኖሪያ ስለሆነ፣ ሚናው ከትምህርት ቤትነት  የበለጠ ይገዝፍብኛል፡፡ ግቢ ዉስጥ ከሰሜንም ይምጣ ከደቡብ ከምራብም ይሁን ከምስራቅ ሁሉም ግን አርብ ምሽት ላይ ስሜታቸው አንድ ነው።  አንድ አርብ ማታ ላይ የሆነዉን ላዉጋችሁ፡  መቸስ ሴቱ ለኦቨር ሲሆን ጨረቃ መስሎ ነው የሚወጣው (ያው ወንዱም አይተናነስም)። የመቀሌ ከተማ እምብርት ላይ አንዱ ጭፈራ ቤት ገባን፤ በሩን ስንከፍት የሚዘል ሰው ቤቱን ሞልቶታል; ባይ የክላስ ልጆች፣ ዞር ብል ሁሉም የግቢዬ ሰዎች! ጎበዝ ብታምኑም ባታምኑም ከግቢ ወደ ግቢ ነው የመጣሁት።

ሰው እንዴት እኩል መዝለል ይችላል?እንደተመካከሩ ሁሉ እንዴት በአንድ አቅጣጯ ሊዘሉ ቻሉ? ቀጭኑም ወፍራሙም ረጅሙም አጭሩም አብሮ እንዳደገ ባንድ ላይ ሲያዜም ላየ አንድ ጐበዝ ዳንሰኛ ያሳደጋቸው ይመስላል።  ረጅም ወንበር ላይ ጠረጴዛ ደገፍ ብየ ቁጭ አልኩ፡፡ ለነገሩ ቁጭ ማለቴ ያጠራጥራል፡፡ እዛ ባለጌ ወንበር ላይ ሆናችሁ ብትታዘቡ የዓለም ኮተት ላያችሁ ላይ እየዘለለ ስለሚመስል ይዞርባችኋል፡  በዚህ ዝላይ መሃል ሲያስተናግድ፣ የያዝኩት ቢራ ከአሁን አሁን ተከሰከሰ በሚል ስጋት ክስት ያለው አስተናጋጅ መጣና ሲያፈጥ ፊትለፊቴ የተገተሩትን ዉስኪዎች ገላምጨ ቢራ አዘዝኩ፡፡ የሥራቸውን ይስጣቸውና፣ “ ከስራ በኋላ ጠጡ ፡ ጎበዝ ከ ጎበዙ ይገባበዙ ” እያሉ ሃሳባችንን ሁሉ ገብስና የገብስ ጭማቂ ላይ እንዲሆን ያደረጉንን አሸን ማስታወቂያዎች አስቤ አንዱን ቢራ ጠራሁለት፡፡  ታላቅ ወንድሙ የጠራዉ ነዉ የሚመስለው እየሮጠ ሄደ።

ተማሪዉ ክላስ ዉስጥ ከሚገናኘዉ የበለጠ እነዚህ ጭፈራ ቤቶች ዉስጥ ይገናኛል፤  የቀን ዉሎም የሚወራዉ እዚሁ ነዉ።   እንደዉም የአርብና የቅዳሜ ምሽት ንጉስ የሆኑ ተማሪዎች እንደዚህ በታላቅ ጩኸት ዉስጥ ሆነው ከፍ ባለ ድምጽ ማዉራትን በደምብ ስለሚለማመዱ  ዲፓርትመንት እየቀየሩ የሙዚቃና የ ቲያትር ክፍል ተማሪ እየሆኑ ነዉ፡፡ ለምን ቢባል ሌሊቱን ጉሮሯቸዉን ሲጠርጉ ስለሚያነጉ በጠራራ ፀሐይ ተራራ አናት ላይ ሄዶ ሲያቅራራ ከሚዉል ተለማማጅ ዘፋኝ በላይ የተሻለ ድምጽ ማዉጣት ስለሚችሉ ነዉ፡፡ እኛ ስንጠጣ ስንጨፍር፤ ስንጠጣ ስንጨፍር እየሞሉት የሚያፈስ ቀዳዳ ታንከር ነዉ የምንመስለው፡፡     የጭፈራ  ቤት  ሽንት ቤቶች እንደ ጉድ ስለሚሽናባቸዉ ሲሚንቶዉ በሚሽናባቸዉ ተማሪ ሽንት ጥንካሬ ልክ ተቦርቡረዋል፡ ከስሚንቶዎቹ በላይ ስንት ነገር ተቦርቡሮ ይሆን? ከ’ኦቨር’ እስከ ‘ሃንግኦቨር’ ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ስንት ህይወቶች ይናዱ ይሆን?

ስራ ስል ምን ትዝ አለኝ የኛ ክላስ ተወካይ(Representative)  በሩ አካባቢ ቆሞ ጭፈራውን ያስነካዋል፡፡  ሁሉም የክላስ ልጅ ከነ ተወካዪ ተገናኘን ማለት ነዉ፡፡ ቆይቶም ጠርሙሱን ከፍ አድርጎ “ አንዴ አንዴ መልዕክት አለኝ   እእእእ  የ እንትን ዲፓርትመንት ሴክሽን  እንትን ተማሪዎች  እዚህ ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል፡፡ ለማን ደዉየ ልናገር እያልኩ  ስጨነቅ እዚሁ ተገናኘን፡፡ በ እዉነት ደስ ብሎኛል    እእእ   የእንትን  ኮርስ ሃንድኣዉት ስለደረሰን እየዉ ሳትጋፉ ቀስ እያላችሁ ከ ዲጄ ዉ  ጀርባ እየመጣችሁ ዉሰዱ” ወገን አንዳንድ መሰረታዊ ሥራዎችም እዚሁ ይጠናቀቃሉ።

“ይዞት ይዞት ጦስሽን… ይዞት ይሂድ ጦስሽን “የሚል ዘፈን መጣ; ሁሉም መጮህ ጀመረ… ሁሉም እንዲሄድላቸዉ የፈለጉት ጦስ ያለ ይመስላል፡፡ ጦሰኛ ሁሉ!በዚህ ጦስ የማባረር ስሜት ላይ እያለን የክላስ ተወካያችን “አንዴ ሌላ መልእክት እ……” ሲል ሁላችንም አፈጠጥንበት  “ኧረ ይሄ ይመቻችኋል፤ እንደዉም ከዘፈኑ ጋር ይሄዳል፡፡ ያ ጦሰኛ አስተማሪ ለነገ ያለዉን ‘ፕረሰንቴሽን’ ሰርዞታል፤ ፈታ በሉ፡፡  ይዞት ይዞት ይዞት ይሂድ…… የምን ፕረዘንቴሽን እ ”።

በጣም ሩቅ በማይባል ጊዜ ዉስጥ እነዚህ ቤቶች አቴንዳንስ እንደሚይዙልን አልጠራጠርም፡  “ ምን አባታችሁ ቆርጧችሁ ነው እ ባለፈዉ የቀራችሁት እ?   እንደውም አሳማኝ ማስረጃ ካላመጣችሁ እዚች ቤት ድርሽ እንዳትሉ” ሳይሉ ይቀራሉ ማን ያዉቃል?ስማቸዉንም እየቀየሩ “ ካምፓስና ዳንስ”፣  “ግቢ ሲለካ ኦቨር ነዉ ለካ”፣  “ የበጋ ድምቀቶቻችን ኑ”፣  “ ያለናንተ ኑሮ” ክለብ መባል ይጀምራሉ።  ከሌሊቱ 11፡30 ታክሲው የዉዝዋዜ ልኡካን ቡድኑን ይዞ ግቢ በር ፊትለፊት ከተፍ አለ፤ ከመጨረሻዉ ወንበር የወረደዉ ፍሬሽ አስተማሪያችን ገድገድ እያለ “አዳሜ ሰኞ የሰጠሁሽን ‘አሳይመንት’ አታምጭና…!” ሲል የሱ ተማሪዎች በአንድነት “F ነዋ የማስታቅፍሽ” መለሱለት።  ሁሌም አርብ፣ ለቅዳሜ አጥቢያ በአንድ ድምጽ የሚሏት መፈክራቸዉ ነች ። ግም ለ ግም…. ………………………………

ቤተልሄም አየለ

Did you find this post helpful? Share with your friends.